Friday, November 26, 2010

የእግዚአብሔር መልስ(1)

የእግዚአብሔር መልስ፡-(1)
                          ልጄ ሆይ!
ላመንክብኝ እምነትህ በይቅርታዬና በፍቅሬ ላይ ጣለው። ብዙ ጊዜ ከአንተ የራቅሁ ይመስልሃል፤ነገር ግን ምን ጊዜም ከአጠገብህ አልለይም፡ በጣም ቅርብህ ነኝ። ሁሉ ነገር ያልተሳካልህ መስሎ የሚታይህ ጊዜም እንዳለ አውቃለሁ፤ ነገር ግን ልጄ ሆይ ምን ያህል እንደምታምንብኝ ትለካበታለህ እንጂ አትጠፋበትም።

ሁኔታዎች አንተ እንዳሰብካቸው እና እንዳቀድካቸው ባይሰምሩልህ ወይም ሳይሳኩልህ ቢቀሩ፤ ወድቀሃል ማለት አይደለም። እንዲያውም ሁኔታዎችን አዝነህና ተክዘህ ልትመዝናቸው አይገባም። ይልቁንም የወደፊቱ ህይወትህ ድቅድቅ ጨለማ የዋጠው መስሎ በሚታይህ ወቅት እንኳን ተስፋ መቁረጥን ከልብህ አውጥተህ ጣለው፤ ፍጹም ፍቅር ፍርሃትን አስወግዶ ይጥላልና።

ያንተ ድርሻ የተቻለህን ማድረግ ብቻ ነው፤ የቀረውን ለእኔ ተወው።

እኔ የፈጠርኩህ እና እጅግ አድርጌ የማፈቅርህ አምላክህ ነኝ። የልብህ ሃሳብና ምኞት ቁልጭ ብሎ ይታየኛል።

ዘለዓለማዊው ደኅንነትህ ትልቁ ፈቃዴ ነው፤ ስለሆነም በዕለት ህይወትህ የተዘበራረቀ ሁኔታ ቢገጥምህም እንኳን በበጎ እለውጠዋለሁ።

ምንም ነገር ከአንተ ብወስድ ጎደለብኝ ብለህ አታጉረምርም፤ የእኔ የምትለው አንዳች ነገር የለምና። እንኳን የአንተ የሆነው ነገር አንተም የእኔ ነህ፤ ሁሉም የእኔ ነው። ካለ እኔ ምንም ነህ፤ ሌላው ቀርቶ ጠንካራው ችግርና መከራ ተከትሎ የሚያመጣውን በረከቴን አስብ።

ይህም ብቻ አይደለም፤ ማብቂያ የሌለው ለአንተ ያለኝን ፍቅር እና በህይወት ዘመን ሁሉ የምትመራበትን ጥበብ እንደምታገኝ አትዘንጋ።

በህይወትህ በእኔ ፈቃድ ያለፈ ሁሉ አንተ አንተን ከምትወደው በላይ ስለምወድህ የሆነ መሆኑን አውቀህ ተቀበለው።

ስለሆነም በምንም ሁኔታ ውስጥ አታጉረምርም። ከሁሉም በላይ የሆነ ፀጋዬ ይጠብቅሃል፤ በርታና በሠላም ተቀበለው ውጤቱም ደስታና በረከት ሆኖ ታገኘዋለህ።

                              (አምላክህ አልፋና ዖሜጋ እግዚአብሔር)

No comments:

Post a Comment