Wednesday, March 9, 2011

የእግዚአብሔር መልስ

                                                          የካቲት 28-2003 ዓ.ም
የእግዚአብሔር መልስ

ልዑለ ባህርይ እግዚአብሔር በሰው ልጆች ውስጥ ያለችውን ነፍስ የፈጠረው በአርአያውና በአምሳሉ ነው። የቀሩትን ፍጥረታት “ይሁን” እያለ በቃሉ ብቻ ካለመኖር ወደ መኖር ሲያመጣ፤ የሰውን ልጅ ግን ከምድር አፈር በመውሰድ በእጆቹ ከፈጠረው በኋላ እስትንፋሱን እፍ በማለት ሕያው እንዲሆን አድርጎታል።በዚህም ምክኒያት የሰው ልጅ ከሌሎቹ ፍጥረታት ሁሉ እጅግ የላቀ መሆኑን ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬያለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች”(መዝ.139፡14) በማለት ገልጾታል።

ጌታችንም በቅዱስ ወንጌል የሰው ልጅ ከፍጥረታት ሁሉ የከበረ መሆኑን ሲገልጽ “የራሳችሁ ፀጉር እንኳን የተቆጠረ ነው”(ሉቃ.12፡7) በማለት እነርሱ የሚችሉትን ብቻ ይስሩ እንጂ ሌላ የሚያሳስባቸውን ነገር ሁሉ በእርሱ ላይ እንዲጥሉ የማጽናኛ ቃል ይነግራቸው ነበር።ሳይታክቱ ዘወትር እርሱን ደጅ እንዲጠኑም “...ለምኑ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ ይከፈትላችሁማል”(ማቴ 7፡7) በማለት ያስተምራቸዋል።

እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ በዘመናችን የብዙ ሰዎች ጥያቄ ግን “እኔ እግዚአብሔርን ዘወትር ደጅ እጠናለሁ፤ እንደ ቃሉም እሄዳለሁ፤ ነገር ግን ለጠየቅሁት ጥያቄ ሁሉ የእግዚአብሔር መልስ የት አለ? እስከመቼስ ልጠብቀው?” የሚል ነው።የእግዚአብሔር መልስ በዘገየ ቁጥርም እነርሱ አላስፈላጊ ወደ ሆነ ጭንቀትና ፍርሃት ውስጥ ይወድቃሉ። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “ሰው ራሱን ከሚጎዳው በቀር አንዳች ነገር አይጎዳውም” እንዳለው እራሳቸውን ለጉዳት ይዳርጋሉ። በመሠረቱ የሚፈራና የሚጨነቅ ሰው የእግዚአብሔርን ፍቅርና ቃልኪዳን የረሳ ሰው ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም።

በዚህ ጽሑፍ የእግዚአብሔር መልስ በምን መልኩ ወደ ህይወታችን ሊመጣ እንደሚችልና እኛም ደግሞ የእርሱን መልስ ስንጠብቅ ምን ማድረግ እንደሚገባን በመጠኑ ለመዳሰስ እንሞክራለንና የጥበብ ባለቤት ጌታ ምስጢሩን ይግለጽልን።

እግዚአብሔር አምላክ ሥራዎቹን የሚሰራበት ረቂቅ ጥበቡ ብዙ ጊዜ ከሰው አስተሳሰብና አመለካከት ጋር አብሮ ሲሄድ አይታይም። “ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ አሳቤም ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው”(ኢሳ 55፡8) እንዳለው የእርሱ አሳብ እና የሰው ልጆች አሳብ የሰማይና የምድር ያህል የተራራቀ ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው የሚጎዳውን ነገር ዛሬ እንዲሰጠው አጥብቆ ሊለምን ይችላል። እግዚአብሔር ግን እንደሚጎዳው ስለሚያውቅ ያንን አስቀርቶ የሚጠቅመውን ነገር አዘግይቶ አስፈላጊ በሆነ ሰዓት ይሰጠዋል። ለዚህ ነው በመጽሐፍ ቅዱስ ጌታ እግዚአብሔር “…ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም”(ኤር. 29፡11) በማለት የሚናገረው። ስለዚህ አሳባችንን ከእርሱ አሳብ ጋር አንድ እንዲሆን መጸለይ እንጂ እርሱን ወደ እኛ አሳብ ለማምጣት መታገል የለብንም ማለት ነው።

እግዚአብሔር አምላክ ገና ሳንለምነው የምንፈልገውን አውቆ የሚሰጠን አምላክ ስለመሆኑና የለመነውንም ነገር እንዳገኘነው እንድንቆጥር እንዲህ በማለት ያስተምረናል “...ስለዚህ እላችኋለሁ፤ የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፤የሆንላችሁማል”(ማር.11፡24)

ይህን ሁሉ የተስፋ ቃል በልባችን ውስጥ ካስቀመጥን፤ የእግዚአብሔር መልስ በእነዚህ በሦስት አይነቶች ወደ ህይወታችን ሊመጣ እንደሚችል መገንዘብ እንችላለን፡-
1. በጠየቅነው ዕለት ወይም በፍጥነት፡- እግዚአብሔር አምላክ ለጠየቅነው ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ሊሰጠን ይችላል። ይህ ከሆነ በእርሱ ላይ ያለንን እምነት እንድናጠነክር ፈቃዱ ሆኗል ማለት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ለጥያቄያቸው ፈጣን ምላሽ የተሰጣቸው ሰዎች አሉ። የመቶ አለቃው ልጁን እንዲፈውስለት ወደ ጌታ ቀርቦ “ጌታ ሆይ...ቃል ብቻ ተናገር ብላቴናዬም ይፈወሳል” (ማቴ.8፡8) ብሎ ሲማጸነው ወዲያውኑ ነበር የመለሰለት። ይህም የሆነበት ምክኒያት የመቶ አለቃው ከመጀመሪያው በጌታ ላይ እምነት ስለነበረው ያንኑ ሊያጠናክርለት ስለፈቀደ ነው። ከጌታ ቀኝ ተሰቅሎ የነበረው ጥጦስም የሆነውን ሁሉ ከተመለከተ በኋላ ክርስቶስ እውነተኛ የባህሪ አምላክ መሆኑን ሲያረጋግጥ “ጌታ ሆይ፡- በመንግስትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ” ብሎ ሲጠይቀው ጊዜ ሳይወስድ ወዲያውኑ ነበር “እውነት እልሀለሁ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ያለው(ሉቃ.23፡43) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን የሰዎችን የአጋንንትንም ልመና በፍጥነት የመለሰበት ጊዜ ነበር። ክርስቶስን አይተው እንዳያጠፋቸው ስለተጨነቁ “ወደ እሪያው መንጋ ስደደን”(ማቴ.8፡31) ብለው ሲለምኑት እንዲገቡ ፈቅዶላቸዋል።

በሽተኞችን፤ ታመው የአልጋ ቁራኛ የሆኑትን፤ የተሸከማቸውን አልጋ ተሸክመው እንዲሄዱ አድርጓቸዋል።እኛስ በህይወታችን ስንት ጊዜ እግዚአብሔር በፍጥነት መልሶልን እኛ ግን እረስተነው ይሆን? ብዙ ሰዎች ታመው አልጋ ላይ ሲሆኑ፤ ወይም በጭንቀት ውስጥ ሲወድቁ እግዚአብሔርን ይማጸኑና እርሱም ከበሽታቸው ሲፈውሳቸው፤ ከጭንቀታቸው ሲላቀቁ  ይረሱታል። በእርግጥ የሰው ልጅ ብዙ ጊዜውን የሚያሳልፈው እግዚአብሔር ወደ ፊት የሚሰጠውን ነገር በማሰብ ወይም ደግሞ እርሱ የከለከለውን ነገር በማሰላሰል እንጅ እስካሁን ስለተደረገው ነገር በማመስገን አይደለም። የተደረገልን ነገር በሙሉ በእኛ ኃይልና ብርታት ከመሰለንና ለእርሱ የሚገባውን ድርሻ ለእኛ የምናደርግ መሆናችንን ካወቀ ወይም ደግሞ በእርሱ ላይ ያለንን ትእግስት መፈተን ከፈለገ እግዚአብሔር ጸሎታችን የሚመልስልን በሚከተለው አማራጭ ይሆናል።

2. ከብዙ ጊዜ በኋላ ዘግይቶ ሊመልስልን ይችላል፡- ይህ የሚሆነው ደግሞ እግዚአብሔር የእኛን ትእግስት መፈተን የፈለገ እንደሆን ነው።ለአብርሃም “በዘርህ አሕዛብ ይባረካሉ” ካለው በኋላ እጅግ ዘግይቶ በእርጅናው ጊዜ ነው ይስሀቅን የሰጠው። የአባታችን የአብርሃም ትእግስትም በዚህ ተፈትኗል። አብርሃም “የእግዚአብሔር መልስ ዘገየብኝ፤ ሌላ አማራጭ ልፈልግ” ብሎ ዘወር ቢል ኖሮ የብዙዎች አባት ባልተባለም ነበር።

እግዚአብሔር መልሱን የሚያዘገዬው ካለ እርሱ ምንም ማድረግ እንደማንችል ሊያስገነዝበን ሲወድ ነው።“ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉም” (ዮሐ15፡5) ብሏልና። አባታችን አዳም ከገነት ከተባረረ በኋላ በራሱ ጥረት ወደ ገነት ለመመለስ ሞክሮ ነበር። እግዚአብሔር ግን ይህ የፈጣሪን ሥራ እንደሚጠይቅ ነግሮት ከአምስት ሽህ አምስት መቶ ዘመን በኋላ ከልጅ ልጁ ተወልዶ እንደሚያድነው ቃል ገባለት። ስለዚህ አባታችን አዳም ያን ሁሉ ዘመን የእግዚአብሔርን መልስ በሲዖል ውስጥ ሆኖ መጠበቅ ነበረበት። በመሠረቱ ይህ ዘመን በሰው ዘንድ የረዘመ ይምሰል እንጂ በእግዚአብሔር አቆጣጠር ግን አምስት ቀን ተኩል ብቻ ነው።አባታችን ሙሴም እስራኤላውያንን እየመራ ከግብፅ ያወጣቸው ለአገልግሎት ከተጠራ ከአርባ አመት በኋላ ሰማኒያ ሲሞላው ነበር። አርባ አመት ሙሉ ግን በሲና በርሃ እጅግ አስቸጋሪ በሆነው ሙቀት ውስጥ የዮቶርን በጎች ይጠብቅ ዘንድ ግድ ነበር።(ዘጸ 4፡18)


3. ምንም ላይመልስልን ይችላል፡- ላቀረብነው ልመና ምንም አይነት ምላሽ ካላገኘን፤ ያ ማለት እኛ ከጠየቅነው ጥያቄ በላይ የተሻለ ነገር አስቦልናል ማለት ነው። እኛ ሰዎች ደካሞች እንደመሆናችን የሚጎዳንና የሚጠቅመንን ለይተን ማወቅ ስለማንችል አጥብቀን የፈለግነው ነገር ምላሹ ከቀረ፤ ሌላ የተሻለ ነገር እግዚአብሔር እያዘጋጀልን እንደሆነ እንመን።

በእርግጥ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ሳያውቁት የሚጠፉበትን ነገር ወይም ደግሞ ሌሎችን የሚጎዳ ነገር ሊለምኑ ይችላሉ። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር በሰዎች ጥፋት ተባባሪ ስለማይሆን “ይህ አይሆንም!” ሊለን ይችላል። የዘብዴዎስ ልጆች እናት ያቀረበችው ልመና ልጆቿን ለመስቀል ሞት የሚያበቃ ስለነበር የተሰጣት ምላሽ “የምትለምኑትን አታውቁም”(ማቴ.20፡22) የሚል ነበር።


ይህን ሁሉ የእግዚአብሔር የአሰራር መንገዶች ከተገነዘብን የእርሱን መልስ ስንጠብቅ ምን ምን ማድረግ ይኖርብናል የሚሉትን ነጥቦች ደግሞ እንደሚከተለው እንመልከት፡-
1.በእምነት መኖር
እግዚአብሔር አምላክ ሰምቶ እንዳልሰማ አይቶም እንዳላዬ ዝም የሚል አምላክ አለመሆኑን ማመን አለብን። እርሱ የሚሰማ የሚመልስም ነው እንጂ።እርሱ የፈጠረን አምላካችን ስለሆነ የልባችን ምኞትና መሻት ቁልጭ ብሎ ይታየዋል።

የእግዚአብሔርን መልስ በእምነት ውስጥ ሆነው ከጠበቁ ሰዎች ውስጥ ምንጊዜም የሚጠቀሰው አባታችን አብርሃም ነው። እግዚአብሔር የማያደርገውን የማይናገር የተናገረውን ደግሞ የማያስቀር አምላክ መሆኑን አብርሃም ጠንቅቆ ያምን ነበር። ስለዚህ የእግዚአብሔር መልስ ቢዘገይም ሊተወኝ ነው ብሎ አልፈራም አልተጨነቀምም።ሰዎች ፍርሃት የሚይይዛቸው እምነታቸው ሲጎድል ነው። ጌታችን ልጁ ለሞተችበት ለምኩራቡ አለቃ “እመን ብቻ እንጂ አትፍራ”(ማር5፡36) ብሎ ያረጋጋው በእርሱ ላይ ያለን እምነት የጸና ይሁን እንጂ ለእርሱ ምንም የሚሳነው ነገር እንደሌለ ሲገልጽለት ነው።

ችግርና መከራ ሲገጥመን እግዚአብሔር እንደሚረዳንና እንዲያውም ለእኛ በጣም ቅርብ የሚሆነው በዚህ ጊዜ መሆኑን ማመን አለብን።ዳንኤል የእግዚአብሔርን መልአክ ያየው እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ በወደደቀበት ወቅት በአንበሶች ጉድጓድ ውስጥ ነው። አናንያ፤አዛርያና ሚሳኤልም መልአኩን ያዩት በእሳት ውስጥ ሆነው ነው። እርሱ የእኛ ጭንቀት ተካፋይ ስለመሆኑ ነቢዩ ኢሳይያስ “በጭንቃቸውም ሁሉ እርሱ ተጨነቀ”(ኢሳ63፡9) በማለት ተናግሯል።እኛ ስንጨነቅ፤በዳር ሆኖ የሚያየን ሳይሆን አብሮን የሚጨነቅ አምላክ እንዳለን ስናስብ ምን ያህል ልባችን በደስታ ይሞላ ይሆን? ስለዚህ የእግዚአብሔርን መልስ ስንጠብቅ በእርሱ ላይ ያለን እምነት የተደላደለና የማይነቃነቅ መሆን ይኖርበታል።(1ቆሮ 5፡58)

2.በተስፋ
ክርስትና በተስፋ የሚኖሩት ህይወት ነው። ክርስቲያንም የሚኖረው ከሚታዩት ነገሮች በላይ ስለሆነ በዚህ አለም እያለ በሚያጣቸው፤ሀላፊ ጠፊ በሆኑ ነገሮች ተስፋ አይቆርጥም። በሥጋዊውም ሆነ በመንፈሳዊ ህይወት የሚያስፈልገንን ነገር ጠይቀን መልሱን የምንጠብቀው በተስፋ ነው። አንዳንድ ጊዜ የወደፊቱ ህይወታችን ድቅድቅ ጨለማ የዋጠው መስሎ የሚታየን ጊዜ ይኖራል። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር አምላክ የተናገራቸውን የተስፋ ቃላት በህሊናችን መድገም በቃላችን ማስታወስ ይኖርብናል። “በህይወትህ ዕድሜ ሁሉ... አልጥልህም፤አልተውህም”(ኢሳ1፡5) “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና...አትፍራ”(ሐዋ.18፡10) እግዚአብሔር አምላክ ለጥቂት ጊዜ የተወን ቢመስልም ለዘለአለሙ ግን ይሰበስበናልና ተስፋችን እርሱ ብቻ ሊሆን ይገባል። እርሱን ተስፋ ያደረገ ሰው ከቶውንም ቢሆን አይወድቅምና።

በአንድ ቀን ውስጥ ጨለማና ብርሃን እንደሚፈራረቁ ሁሉ በሰው ልጅ ህይወትም ፈተናና ደስታ ይፈራረቃሉ።ስቅለት እንዳለ ሁሉ ፋሲካም ይኖራል፤ ስለዚህ በስቅለት ያዘነ የተከዘ ሰው በፋሲካው ደግሞ ይደሰታል። በስቅለት ካላለፉ በቀር ስለፋሲካ ማውራት እንደሚከብደው ሁሉ ደስታም ያለ ፈተና ሊመጣ አይችልም። ለዚህ ነው ሐዋሪያው ያዕቆብ በመልእክቱ “ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት”(ያዕ.1፡2) ያለው። ይህ የተስፋ ቃል የተነገረው ጽኑ የሆነው መከራችን አስከትሎ የሚያመጣው በረከት ስላለ ነው። የገጠመን አስጨናቂ ፈተና ደስታን እንደሚያመጣልን ተስፋ የምናደርግ ስንቶቻችን እንሆን?

3.በፍቅር
ቀድሞ ስናደርግ እንደነበረው ሰውንም እግዚአብሔርንም መውደድ፤ ለሁሉም የሚገባውን ክብር መስጠት የእርሱን መልስ ስንጠብቅም መቀጠል አለበት። ዮሴፍ ያለ ኃጢአቱ ስለ ታሰረ፤ በእስር ቤት ሆኖ የእግዚአብሔርን መልስ ይጠብቅ ነበር።ነገር ግን በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ እንኳን በእስር ቤት ውስጥ እግዚአብሔርንም ሰውንም በፍቅር ያገለግል ነበር እንጂ ድሮ ያደርግ የነበረውን ነገር አላቋረጠም። ብዙ ሰዎች ግን የጸሎታቸው ምላሽ ሲዘገይ ቀድሞ ያደርጉ የነበሩትን ነገሮች እርግፍ አድረገው ይተዋሉ። በፊት ከቤተ ክርስቲያን የማይለዩት፤ በቀን ሁለት ጊዜ የሚጸልዩት አሁን ጨርሰው ይጠፋሉ፤ ከጸሎትም ይሸሻሉ። ምክኒያታቸውን ሲገልጹም እግዚአብሔር እንደረሳቸው፤ ለጸሎታቸውም ምላሽን እንዳጡ ይናገራሉ። እነዚህ ሰዎች የዘነጉት ነገር ቢኖር እግዚአብሔር አምላክ ማንንም እንደማይረሳ ነው። “ሴት ከማህፀንዋ ለተወለደው ሕፃንዋ እስከማትራራ ድረስ ልትረሳ ብትችልም” እርሱ ግን ፈጽሞ ሰው እንደማይረሳ የተናገረ አምላክ ነው።(ኢሳ.49፡15) የተናገረውን የማያስቀር አምላክ በመሆኑም ሙሴ መልኩን ለማየት ተመኝቶ ሞት ቢቀድመውም ከሞት አስነስቶ ከመቃብር አውጥቶ የተመኘውን ፈጽሞለታል። ለዚህ የፍቅር አምላክ እኛም የሚፈለግብንን ምስጋና ልናቀርብለት ይገባል እንጂ የእግዚአብሔር መልስ ዘገዬ ብለን በእርሱ ላይ ልንነሳሳ አይገባም። ለበጎ ቢያዘገየውም ልመናችንን አያስቀረውምና።   

ስለዚህ ሰማይና ምድር ቢያልፉም እነርሱ ጸንተው የሚኖሩትን፤ ሦስቱን የክርስትና ሃይማኖት የእምነት ምሰሶዎች “እምነትን፤ተስፋን፤ፍቅርን”(1ቆሮ.13፡13) አንግበን፤ከሁሉም በሚበልጠው በፍቅር ከአምላካችን ጋር ተሳስረን፤  ከፊት ለፊታችን የሚጠብቀንን ሩጫ በትእግስት እንሩጥ። ለአባቶቻችን የተለመነ አምላክ ለእኛም መሻታችን ይፈጽምልናልና እመነታችንን አጽንተን የ እርሱን መልስ እንጠብቅ። እርሱን ተስፋ አድርጎ ያፈረ የለምና ተስፋችንንም በእርሱ ላይ እንጣለው። “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ያለቀ የተቆረጠ ነገርን በምድር መካከል ሁሉ ይፈጽማል”(ኢሳ 10፡23) ከእኛ የራቀ ቢመስለንም ምን ጊዜም ከአጠገባችን መሆኑንም አንዘንጋ። አንድያ ልጁን ሳይሳሳ የሰጠን አምላክ የእኛን ልመና እነዴት አይቀበለን?

ወስብሃት ለእግዚአብሔር።

ዲን. ፍቅረሥላሴ አቢይ
(ስቶክሆልም፤ የካቲት 30፤2003)






Saturday, December 11, 2010

ተስፋ ለቆረጠው ሰው የመጨረሻው ተስፋ

                                             ሕዳር 30፤2003 ዓ.ም
ተስፋ ለቆረጠው ሰው የመጨረሻው “ተስፋ”ዮሐ.9፡ 1-41

“የጻድቃን ምርኩዝ፤ ለተሰደዱት ተስፋቸው ለሚታወኩት ፀጥታቸው አንተ ነህ”(ቅዳሴ እግዚእ ቁጥር 20)

ከሕዳር 6 እስከ ታህሳስ የመጀመሪያው ሳምንት ድረስ የሚገኘው ወቅት “አስተምህሮ/ምህረት አደረገ” ተብሎ ሲጠራ በዚህ ወቅት መድኅነ ዓለም ክርስቶስ ድውያንን መፈወሱ፤ ዕውራንን ማብራቱ፤ሽባውን መተርተሩ እና በአጠቃላይ በመዋዕለ ሥጋዌው የሰራቸው ግሩም ተአምራቶቹ በሰፊው የሚዘከርበት ወቅት ነው።
ከዚህ አንጻር ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የሚመጣውን እሁድ በክርስቶስ ድንቅ ተአምር ፈውስን ከአገኙት ሰዎች መካከል “ዘዕውሩ ተወልደ/ ዕውር ሆኖ የተወለደው” የተባለው ሰው የሚታሰብበት ቀን ነው።

የሰው ልጆች በሕይወታቸው ውስጥ በሚያጋጥሟቸው የተለያዩ ፈተናዎች የተነሳ ተስፋ ሊቆርጡ ወይንም ተስፋቸው ተሟጦ ሊያልቅ ይችላል። ከእነዚህም ውስጥ ሰዎች በሥጋዊና በመንፈሳዊ ሕይወታቸው በሚያጋጥሟቸው ፈተናዎች ፈጽመው ተስፋ መቁረጥ ደረጃ ላይ ሲደርሱ ማየት እጅግ በጣም የተለመደ ነው። በተለይ “ንስሃ መግባትና ወደ እግዚአብሔር መቅረብ” ተስፋ ያስቆረጣቸው፤ እንዲህ አይነቱ ነገር እንዲነሳባቸው የማይፈልጉ፤ የልባቸውን በር ዘግተው የተቀመጡ ብዙዎች አሉ።

ቅዱስ አትናቴዎስ በሃይማኖተ አበው ላይ ... “ሰይጣን ምን አለበት በሚል መንፈስ ኃጢአት እንድንሰራ ይገፋፋንና ከዚያ በኋላ ደግሞ እንዴት ይህን ሰርተህ ወደ እግዚአብሔር ቤት ትሄዳለህ? እያለ ከእግዚአብሔር እንድንርቅ ያደርገናል”... እንዳለ ዛሬ ብዙ ሰዎች በዚህ መንፈስ ተወስደው እራሳቸውን እንደደካማ ቆጥረው፤ በእነርሱ ውስጥ የሚሰራውን የእግዚአብሔርን መንፈስ ከነመኖሩም ዘንግተው፤ ተስፋ መቁረጥ ደረጃ ላይ የደረሱ አሉ። ይህ ግን የክርስቲያን ጠባይ እንዳልሆነ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ በማለት ነበር የገለጸው... “በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፡ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም”።(2ቆሮ4፡9)

በዮሐንስ ወንጌል በምዕራፍ ዘጠኝ ላይ የምናገኘው ዓይነ ስውር ሆኖ በተወለደው ሰው ታሪክ አንድ በግልጽ መማር የምንችለው ነገር አለ። ይኸውም ሰውየው ለመዳን የነበረው ተስፋ “ምንም” የሚባል ቢሆንም የመጨረሻውን ተስፋ ያገኘው ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ መሆኑን ነው።
በዚህ ጽሑፍም የዚህን ሰው ታሪክ በአጭሩ ለመዳሰስ እና ከሰውየውም ምን መማር እንዳለብን ለማየት እንሞክራለንና የጥበብ ባለቤት ጌታ እግዚአብሔር ማስተዋሉን ይግለጽልን።

ዮሐ. 9፡1 “ሲያልፍም ከመወለዱም ጀምሮ ዕውር የሆነውን ሰው አየ” ይላል። ይህ ሰው እንደሌሎቹ ዓይነ ስውራን ዓይን ኖሮት ዓይኖቹ የታወሩ ሆነው አይደለም። ከነጭራሹ ዓይን የሚባል ነገር የለውም። ግንባሩ ላይ የሚታይ ነገር ቢኖር ሁለት ክፍት ነገሮች ሆነው ውስጣቸው ምንም ነገር የሌለበት ነበር። ስለዚህ ይህ ሰው ማየት እንዲችል “ከተአምር በላይ” የሆነ ነገር ያስፈልገው ነበር ማለት ነው። ምክኒያቱም እንደሌሎቹ ዓይን ኖሮት ማየት ቢሳነውና ቢፈወስ “በተአምር ዳነ” ሊባል ይችላል። ይህ ሰው ግን ዓይን የሚባል ነገር የለውም። በአጠቃላይ ተስፋ የሌለው ነበር ማለት ይቻላል። ይህ ሰው በተለያዩ ምክኒያቶች እግዚአብሔርን ማግኘት ያልቻሉ ሰዎችን ሊወክል ይችላል። ይህ እንግዲህ ተስፋ የማጣት ምሳሌ ነው ማለት ነው። ምክኒያቱም ሰውየው የፈለገውን ያህል ርቆ ሄዶ ተስፋ ቢያደርግ፤ “ማየትን” ግን በጭራሽ ሊያስበው እንኳን እንደማይችል ግልጽ ነው፤ ለማይት የሚያስፈልገው ትንሹ መስፈርት “ዓይን” የለውምና።

ስለዚህም የናዝሬቱ ኢየሱስ “ድውያንን ይፈውሳል፤ ዕውራንን ያበራል” የሚሉትና በወቅቱ የብዙዎችን ትኩረት የሳቡት ጉዳዮች ለዚህ ሰው ትርጉም ሊኖራቸውና ሮጦ ሄዶ መፍትሄ ሊፈልግባቸው የሚችሉ አልነበሩም። ምክኒያቱም ከዚህ በላይ እንደተገለጸው እርሱ የሚሻው “ተአምር” ሳይሆን ከዚያ በላይ የሆነ ነገር ነውና።

ሰውየው ተስፋ ቆርጦ ቁጭ ቢልም “የተስፋ ተስፋ” የሆነው ጌታችን ወደ እርሱ ቀርቦ እንዳነጋገረው እና በድንቅ ተአምራቱ እንደፈወሰው እናነባለን።
በዚህ የጭንቅ ሰዓት የዓለም ሁሉ ብርሃን የሆነው ጌታ “በምራቁ ጭቃ ቀብቶ ሂድና በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ አለው” እዚህ ላይ የታየው የጌታችን እና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ፈጣሪ መሆንን ነው። ልክ አጋእዝተ ዓለማት ሥሉስ ቅዱስ በኦሪት ዘፍትረት 1፡26 ላይ “ሰውን ..እንፍጠር” ብለው አዳምን ከጭቃ እንደፈጠሩት ሁሉ አሁንም ጌታችን የዚህን ሰው ዓይኖች ከጭቃ እንደፈጠረለት እናያለን።

ከእግዚአብሔር የባህሪ ልጅ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ይህንን ሊያደርግ የሚችል ማነው? ምን አይነት ተአምር ቢፈጠር ነው? የሌለን ነገር አስገኝቶ መፈወስ የሚቻለው ፈጣሪ ብቻ ነውና። ይህ ተአምር የመለኮት እና የሥጋ ተዋህዶ የታየበት ድንቅ ተአምር ነው። ወደ መሬት እንትፍ ያለው ምራቅ መለኮት የተዋሃደው ባይሆን ኖሮ ዓይን መፍጠር ባልቻለም ነበርና። ሕይወት በሌለው ነገር ላይ ሕይወትን መዝራት ተአምር ብቻ ነው ብለን የምናልፈው አይደለም፤ ከዚያም በላይ ነው እንጂ፤ምክኒያቱም መፍጠርን ይጠይቃልና። ለዚህም ነው ጌታን “ተስፋ ለቆረጠው ሰው የመጨረሻው ተስፋ አንተ ነህ” የምንለው፤ የማየት አንዳች ተስፋ ያልነበረው ሰው አሁን ወደ ማየት ተሸጋግሯልና።

በዚህ ምዕራፍ የምንማረው ትልቁ ምስጢር ደግሞ ጌታ የሥጋን ፈውስ ብቻ ሳይሆን የነፍስንም የሚሰጥ መሆኑን ነው። ይህንን ሰው ዓይኑን ካበራለት በኋላ የነፍሱንም እንዲያስብ አስገንዝቦት ነበር። ዮሐ 9፤35 “ኢየሱስም ወደ ውጭ እንዳወጡት ሰማ..”
እዚህ ላይ የምናየው ጌታ አድኖት ብቻ ዝም አላለም የነፍሱንም ድኅነት ሙሉ ለሙሉ እስኪያገኝ ይከታተለው ነበር። “በእግዚአብሔር ልጅ ታምናለህን?” ብሎ ሲጠይቀው እርሱም “በእርሱ አምን ዘንድ ማነው?” ብሎ መለሰ፤ ምክኒያቱም ሲፈውሰው ማይት አይችልም ነበርና ማን እንዳዳነው አላወቀም ነበር። ዛሬም እኛ ሳናውቀው በሕይወታችን ውስጥ እግዚአብሔር የሚሰራው ብዙ ድንቅ ነገሮች እንዳሉ መዘንጋት የለብንም። በመጨረሻም የነፍሱን ድኅነት አገኘ፡ አድርግ እንደተባለውም በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ አመነ።ምዕራፉ ሲጀምር ቁጭ ብሎ ይለምን የነበረ ሰው አሁን ወደ ማየትና በጌታ ወደ ማመን ተሸጋገረ።

ይህ ሰው ጌታችን ለመጀመሪያ ጊዜ “ልትድን ትወዳለህን?” ብሎ ያልጠየቀው ሰው ነው። ምክኒያቱም አልታመመም ነበርና። ምን አልባት ጠይቆት ቢሆን ኖሮ ግን መልሱ “መዳን አልፈልግም...አልታመምኩመና... የሞትኩ ነኝ እንጂ” የሚል ሊሆን እንደሚችል ከሁኔታው መገመት ይቻላል።

ይህ ሰው የተስፋ ጭላንጭሉ ተሟጦ ተስፋ ቆርጦ በነበረበት ሰዓት ጌታችን የሚከተለውን አደረገ፡-
1.  ወደ ሰውየው ሄደ፡- ይህ ሰው ከዚህ በፊት ክርስቶስ በድንቅ ተአምሮቶቹ እንደፈወሳቸው ሰዎች (እንደ ለምጻሙ ሰው፡ 12 ዓመት ደም ይፈሳት እንደነበረችው ሴት) ክርስቶስን ፍለጋ አልሄደም ነበር። “ልድን አልችልም” ብሎ ተስፋ ቆርጦ ቁጭ ብሏል እንጂ።
2.  ሲያድነው (አዲስ ዓይን ሲፈጥርለት) “ልትድን ትወዳለህን?” ብሎ አልጠየቀውም፡- ምክኒያቱም ማዕመረ ኅቡአት ጌታችን የልቡንና የሚያስበውን ብሎም ሊመልስ የሚችለውን ስለሚያውቅ እንደሌሎቹ በሽተኞች ይህንን ጥያቄ አላቀረበለትም።
3.  ጌታ አድኖት ብቻ ዘወር አላለም፤ ፈለገውም እንጂ፡- የሥጋ ብቻ ያይደለ የነፍስም ድኅነት የገኝ ዘንድ ፈልጎት ነበር፤መጨረሻ ላይ አገኘው። ጌታችን የፈወሳቸውን በሽተኞች መጨረሻቸው እንዲያምርና የነፍሳቸውንም ነገር እንዲያስቡ ለማስገንዘብ ይከታተላቸው ነበር።
4.  የነፍሱንም ዓይን (መንፈሳዊ ዓይኑን) አበራለት፡- ፈጽሞ “አምናለሁ” እስከሚል ድረስ አነጋገረው። የዚህ ሰው ድኅነት ከሌሎቹ የሚለየው የነፍስም የሥጋም በመሆኑ ነው። ብርሃኑን ያገኘው ከውስጥ ወደ ውጭ ነበር። በወቅቱ ከበው  “ያዳነህ ማነው?” በሚል በጥያቄ ያጣድፉት የነበሩት ጸሐፍት ፈሪሳውያን ግን ፡ውስጣዊ ዓይኖቻቸው የታወሩ ነበሩ። ለዚህ ነው ክርስቶስ ዓይነ ስውርነታቸውን እንኳን ባለማወቃቸው “እናያለን ትላላችሁ፡ነገር ግን አታዩም” የሚላቸው። ሰላሳ ስምንት ዓመት አልጋ ላይ ተኝቶ የነበረው ሰው ከዳነ በኋላ መጨረሻው አላመረም ነበር። “በሰንበት ቀን አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለኝ ይህ ነው” ብሎ ክርስቶስን አሳልፎ ሰጥቶታልና። ለእርሱም ቢሆን ግን ጌታ “የባሰ እንዳያገኝህ ዳግመኛ አትበድል” ብሎ አስጠንቅቆት ነበር።(ዮሐ. 5፡1-15) ይህ ዓይነ ስውሩ ሰው ግን ሳያየው ስላዳነው እና ማን መሆኑንም ስላላወቀው ጌታ ክርስቶስ አጥብቆ ጸሐፍት ፈሪሳውያንን ይከራከራቸው ነበር።

ይህን ሁሉ ካደረገ በኋላ ነው እንግዲህ ሰውየው ተስፋ ከመቁረጥ ተነስቶ እግዚአብሔርን ወደ ማመንን የተሸጋገረው። ምንም ካለማየት የእግዚአብሔርን ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ማየት መምጣት እንዴት የሚያሰደንቅ ተአምር ነው? ለመጀመሪያ ጊዜ በዓይኑ ካያቸው ሰዎች ውስጥ አንዱ ጌታችን ነው? ገና “ሀ” ብሎ ማየት ሲጀምር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ማየት ምንኛ መታደል ነው?

ይህ ሰው ይህን ወደ መሰለ መባረክ እንዲመጣ፡ በክርስቶስ እጅ እንዲዳሰስ የሰራው ሥራ ምንድነው? ብለን ብንጠይቅ መልሱ “ተስፋ ቢስ” መሆኑ ብቻ ነው። እንዲህ ተስፋ ለቆረጡ ሰዎች ብቸኛውና አንድና አንድ መፍትሔው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው።

ጌታ ወደ እርሱ የመጡትን ብቻ ሳይሆን እርሱም ተስፋ ወደ ቆረጡት፤ በምንም መልኩ ወደ እርሱ መምጣት ወደ ማይችሉት ሰዎች ዘንድ ሄዶ እንደሚያድናቸውና ተስፋቸውን እንደሚያለመልምላቸው በዚህ እንረዳለን። ይህን ሰው ከፈጠረው ከእግዚአብሔር በቀር አንዳች ተስፋ አልነበረውምና ነው ጌታ ወደ እርሱ ሄዶ የፈወሰው።

በመጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ አጋጣሚዎች ተስፋ ቆርጠው የነበሩ ሰዎችን ማንሳት ይቻላል። ለምሳሌ አንዱና ተስፋ ሊቆርጥ አይችልም ብለን የምንገምተው ሰው ቅዱስ ዳዊት ነው። ቅዱስ ዳዊት ልበ አምላክ እስከመባል የደረሰ፤ እግዚአብሔር ሊያደርግ ያሰበውን አስቀድሞ የሚነግረው፤ ጌታ ከመወለዱ አስቀድሞ ከልደቱ እስከ እረገቱ ብሎም ዳግም ምጻቱ ድረስ በዝርዝር የጻፈ ታላቅ ነቢይ ነው። በአንድ ወቅት ግን የሰው ሚስት ከመቀማቱም በላይ ንጹሑን ኦርዮንን ወደ ጦርነት ልኮ አስገደለ። በዚህ ድርጊቱም እጅግ ከመጸጸቱ የተነሳ ከእርሱ የማይጠበቀውን በመስራቱ “ተስፋ ቆረጠ”። በቀን ሰባት ጊዜ አመሰግንሃለሁ ያለ ቅዱስ ዳዊት አሁን ሲሳሳት ሀዘን ወደ ልቡ ጠልቆ ገባ። እኛ እራሳችንን በቅዱስ ዳዊት ቦታ ብናስቀምጥ ምን እንል ይሆን? ምንአልባት “...ወደ ቤተ ክርስቲያን አብዝተን እንሄዳለን ተግተን እንጸልያለን...” እንል ይሆናል። ቅዱስ ዳዊት ግን “አቤቱ ንጹህ ልብን ፍጠርልኝ” (መዝ50፡10) ብሎ ነበር የጸለየው። “ስብራቴን ጠግንልኝ፤ የበዛውን ኃጢአቴን ደምስስልኝ” አይደለም ያለው፤ ፍጠርልኝ አለ እንጂ። ከምንም በላይ የፈጣሪ ሥራ መግባት እንዳለበት ተገንዝቦ ነው ይህንን ያለው።

እኛም ዛሬ በተለያየ መልኩ ጌታን ብናስቀይመውም፤ ያ የሰራነው በደል እጅግ የበዛ ቢመስለንም፤ እንደጋና ወደ ቤቱ መመለስ የማንችል መስሎ ቢታየንም..ልክ እነደ ቅዱስ ዳዊት “ንጹህ ልብን ፍጥርልን” ብለን ብንጸልይ እርሱ የታመነ አምላክ ነውና ለዚህ ዓይነስውር ሰው አዲስ ዓይን እንደፈጠረለት ሁሉ ለእኛም ይፈጥርልናል። “ጌታችን ታላቅ ነው ኃይሉም ታላቅ ነው፤ ለጥበቡም ቁጥር የለውም” መዝ. 146፡5

ወደ ቀደመ ነገራችን ስንመለስ ይህ ዓይነስውር ሰው ለምን “ዓይነስውር ሆኖ ተወለደ?” የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ይቻላል። መልሱም እዚሁ ምዕራፍ ላይ ተጽፎ እንደሚገኘው “የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ እንዲገለጽ ነው” (ዮሐ. 9፡3) ይህም ማለት እግዚአብሔር አምላክ ፍጥረታትን የሚፈጥረው ለሁለት ምክኒያቶች ነው፡ ለአንክሮ እና ለተዘክሮ። ለአንክሮ ማለት የእርሱን የእጁን ሥራ አይተን እንድናደንቅ ማለት ሲሆን ለተዘክሮ ማለት ደግሞ ፍጥረታቱን አይተን እርሱን(ፈጣሪን) እንድናስታውስ ማለት ነው።

ከዚህ አንጻር ይህ ሰው ዓይነስውር ሆኖ የተወለደው የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ እንዲገለጽ ምክኒያት ስለሆነ ነው። ለዚህ ነው እርሱ ራሱ ይከራከሩት ለነበሩት ጸሐፍት ፈሪሳውያን “ዕውር ሆኖ የተወለደውን ዓይኖቹን ማንም እንደከፈተ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ አልተሰማም”(ዮሐ 9፡32) ብሎ የመሰከረው።

ሌላው ዓይነስውር ሆኖ እንዲወለድ የሆነበት ምክኒያት ጌታ የበለጠ ጸጋ ሊሰጠው ስለወደደ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልዕክቱ “ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን”(ሮሜ. 8፡28) እንዳለ የዚህ ሰውም ዕውር ሆኖ መወለድ ለበጎ ነበር የሆነለት። ወደ መንግስተ ሰማያት ሄደን ይህን ሰው ብናገኘውና “እንደገና ብትወለድ እያየህ መወለድ ትፈልግ ነበር ወይ?” የሚል ጥያቄ ብናቀርብለት መልሱ “አንድ ጊዜም ብቻ ሳይሆን አሥር ጊዜም ቢሆን መወደለድ የምፈልገው ዓይነስውር ሆኜ ነው..ጨለማውንም ወድጄዋለሁ የብርሃኑን መልካምነትና ታላቅነት አይቼበታለሁና” ማለቱ የማይቀር ነው። በጌታችን በኢየሱስ እጅ የተዳሰሰ ዓይን የተፈጠረለት ሰው! ከዚህ ውጭ ምን ሊል ይችላል?

ውድ የክርስቶስ ቤተሰቦች! ዛሬም እኛ በድቅድቅ ጨለማ ያለን ብንመስልም ከዚህ ጨለማ ጀርባ ብርሃኑ እንደሚበራ ማመን አለብን። በዚህ ውስጥ እንድናልፍ ያደረገን ጌታ የብርሃኑን ታላቅነት እንድናደንቅና ቸርነቱን እንድናጣጥመው ስለሚፈልግ ነው። ስለዚህ ብርሃኑን እስከሚያበራልን ድረስ በቤቱ ውስጥ ሆነን በትእግስት እንጠብቀው። “ወዘአዝለፈ ትእግስቶ ውእቱ ይድኅን፤ እስከ መጨረሻው የሚጸና እርሱ ይድናል”(ማቴ 24፡13) ደግሞም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እስከሆነ ድረስ ጨለማውንስ የምንፈራው ለምንድነው? ቅዱስ ዳዊት እኮ “በሞት ጥላ መካከል እንኳን ብሄድ፤አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉውን አልፈራም” (መዝ.22፡4) ነው ያለው።
በእርግጥ በእኛና በቅዱሳን መካከል ያለው ልዩነት እግዚአብሔርን የምናይበት ዓይን እንደመሆኑ፤ እኛም ስንጸልይ “አቤቱ ጌታ ሆይ !! አንተን የምናይበት ዓይን ፍጠርልን” ብለን እንቅረብ። እርሱን የምናይበት ዓይን ቢኖረን ኖሮ፤ እግዚአብሔር አጠገባችን ሆኖ ቅዱሳን በዙሪያችን መኖራቸውን እያሰብን በእነርሱ ፊት ኃጢአትን ለመስራት አንደፍርም ነበርና። ስለዚህ ዓይነስውር ሆነን ቀርበን ዓይን ፍጠርልን እንበለው እንጂ እንደ አይሁድ “እያዩ እንደማያዩ” አንሁን። “የማያዩ እንዲያዩ፤ የሚያዩም እንዲታወሩ እኔ ወደዚህ ዓለም መጣሁ” (ዮሐ.9፡39) የተባሉት አይሁድ በልባቸው እንደሚያዩ ሆነው ጌታን በመቅረባቸው ነበር። እነርሱ ግን ሥጋዊው ዓይናቸው ያያል እንጂ ዓይነ ልቡናቸው የታወረ መሆኑን አላወቁትም ነበር።

በመጨረሻም በቅዳሴ እግዚእ ላይ ተጽፎ እንደሚገኘው “አቤቱ የዕውቀት ዓይኖችን ስጠን ዘወትር አንተን ብቻ ያዩ ዘንድ፤  ጆሮቻችንም የአንተን ብቻ ቃል ይሰሙ ዘንድ ሰውነታችን ከጸጋህ ከጠገበች ዘንድ ንጹህ ልቡናን ፍጠርልን” እያልን ልንጸልይ ይገባናል። ሰይጣን በሰራነው ኃጢአት ተስፋ እንዳያስቆርጠን አጥብቀን ልንዋጋው ያስፈልጋል። ምንም የማይሳነው እግዚአብሔር ለዚህ ተስፋ ለቆረጠው ሰው ዓይንን እንደፈጠረለት ሁሉ ለእኛም አዲስ ልብን ሊፈጥርልን ቃል ገብቷል። “አዲስ ልብ እሰጣቸዋለሁ አዲስ መንፈስም በውስጣቸው አኖራለሁ” (ሕዝ.36፡26) ይህን የተናገ እግዚአብሔር ለቃሉ ታማኝ ነውና ተግተን ዘወትር እንለምነው፤ እርሱም ጆሮውን ወደ እኛ ዘንበል አድርጎ ልመናችንን ይሰማናል፤ አዲስ የእግዚአብሔር ሰራዊት ሆንን በፊቱ እንድንቆም በቸርነቱ ያግዘናል። “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በምድር ውስጥ ያለቀና የተቆረጠ ነገርን ይቀጥላል” (ኢሳ. 10፡23)

ወስብሃት ለእግዚአብሔር!

ዲን.ፍቅረሥላሴ ዐቢይ

Friday, November 26, 2010

የእግዚአብሔር መልስ(2)

                         የእግዚአብሔር መልስ፡-(2)          
                   ልጄ ሆይ!
•ጌታን ስትጠብቀው ቢዘገይብህ እንዲህ በል…
* * *
“በእግርጥ ጌታ ይመጣል …መቼ እንደሚመጣ ግን አላውቅም። ከእኔ የሚጠበቀው የሚመጣበትን  ቀን ማወቅ ሳይሆን እንደሚመጣ ማመን ነው።”
* * *
•በመከራና በፈተና ውስጥ ስትሆን ደስታ እንዳይርቅህ እንዲህ በል…
                         * * *
“መከራና ፈተና በአማኝ ውስጥ ደስታን እንጂ ጭንቀትን አይፈጥሩም!!”
                         * * *
•ተስፋ እንዳትቆርጥ ይህን መዝሙር ከዳዊት ጋር ዘምር…
                         * * *
“እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ በርታ ልብህም ይጽና እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ” መዝ.26፡14
·        ችግር ሲገጥምህ እንዲህ በል…
                   * * *
“እኔ ባላውቅም ከዚህ ችግር በስተጀርባ አንድ በጎ ነገር አለ…ማንኛውም አይነት መጥፎ ነገር ቢኖርም እንኳን አንተ ቸር እና ሰውን የምትወድ አምላክ ስለሆንክ ለበጎ አድርገህ ትቀይረዋለህ”
                     * * *
·        ሰይጣን በኃጢአትህ ተስፋ እንዳያስቆርጥህ በልብህ እንዲህ በል…
“በሰዎች ዘንድ ያለው ኃጢአት ሁሉ ከእግዚአብሔር ቸርነትና ምህረት ጋር ሲነጻጸር በውቅያኖስ ውስጥ እንደተጣለ ፍንጣቂ ጭቃ ይቆጠራል”
·        ለጸሎት በቆምክ ጊዜ ማለት ስላለብህ ነገር ብዙ አትጨነቅ…
                           * * *
“እግዚአብሔር አምላክ ገና ፊቱ ስትቆም ቃላቶችህን ከመናገርህ በፊት ምን ማለት እንደፈለግህ የልብህን ያውቃልና፤ ሳትለምነው ምን እንደምትሻ ያውቃልና…”
                           (አምላክህ አልፋና ዖሜጋ እግዚአብሔር)