Saturday, November 26, 2011
Monday, November 14, 2011
Wednesday, March 9, 2011
የእግዚአብሔር መልስ
የካቲት 28-2003 ዓ.ም
የእግዚአብሔር መልስ
ልዑለ ባህርይ እግዚአብሔር በሰው ልጆች ውስጥ ያለችውን ነፍስ የፈጠረው በአርአያውና በአምሳሉ ነው። የቀሩትን ፍጥረታት “ይሁን” እያለ በቃሉ ብቻ ካለመኖር ወደ መኖር ሲያመጣ፤ የሰውን ልጅ ግን ከምድር አፈር በመውሰድ በእጆቹ ከፈጠረው በኋላ እስትንፋሱን እፍ በማለት ሕያው እንዲሆን አድርጎታል።በዚህም ምክኒያት የሰው ልጅ ከሌሎቹ ፍጥረታት ሁሉ እጅግ የላቀ መሆኑን ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬያለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች”(መዝ.139፡14) በማለት ገልጾታል።
ጌታችንም በቅዱስ ወንጌል የሰው ልጅ ከፍጥረታት ሁሉ የከበረ መሆኑን ሲገልጽ “የራሳችሁ ፀጉር እንኳን የተቆጠረ ነው”(ሉቃ.12፡7) በማለት እነርሱ የሚችሉትን ብቻ ይስሩ እንጂ ሌላ የሚያሳስባቸውን ነገር ሁሉ በእርሱ ላይ እንዲጥሉ የማጽናኛ ቃል ይነግራቸው ነበር።ሳይታክቱ ዘወትር እርሱን ደጅ እንዲጠኑም “...ለምኑ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ ይከፈትላችሁማል”(ማቴ 7፡7) በማለት ያስተምራቸዋል።
እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ በዘመናችን የብዙ ሰዎች ጥያቄ ግን “እኔ እግዚአብሔርን ዘወትር ደጅ እጠናለሁ፤ እንደ ቃሉም እሄዳለሁ፤ ነገር ግን ለጠየቅሁት ጥያቄ ሁሉ የእግዚአብሔር መልስ የት አለ? እስከመቼስ ልጠብቀው?” የሚል ነው።የእግዚአብሔር መልስ በዘገየ ቁጥርም እነርሱ አላስፈላጊ ወደ ሆነ ጭንቀትና ፍርሃት ውስጥ ይወድቃሉ። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “ሰው ራሱን ከሚጎዳው በቀር አንዳች ነገር አይጎዳውም” እንዳለው እራሳቸውን ለጉዳት ይዳርጋሉ። በመሠረቱ የሚፈራና የሚጨነቅ ሰው የእግዚአብሔርን ፍቅርና ቃልኪዳን የረሳ ሰው ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም።
በዚህ ጽሑፍ የእግዚአብሔር መልስ በምን መልኩ ወደ ህይወታችን ሊመጣ እንደሚችልና እኛም ደግሞ የእርሱን መልስ ስንጠብቅ ምን ማድረግ እንደሚገባን በመጠኑ ለመዳሰስ እንሞክራለንና የጥበብ ባለቤት ጌታ ምስጢሩን ይግለጽልን።
እግዚአብሔር አምላክ ሥራዎቹን የሚሰራበት ረቂቅ ጥበቡ ብዙ ጊዜ ከሰው አስተሳሰብና አመለካከት ጋር አብሮ ሲሄድ አይታይም። “ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ አሳቤም ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው”(ኢሳ 55፡8) እንዳለው የእርሱ አሳብ እና የሰው ልጆች አሳብ የሰማይና የምድር ያህል የተራራቀ ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው የሚጎዳውን ነገር ዛሬ እንዲሰጠው አጥብቆ ሊለምን ይችላል። እግዚአብሔር ግን እንደሚጎዳው ስለሚያውቅ ያንን አስቀርቶ የሚጠቅመውን ነገር አዘግይቶ አስፈላጊ በሆነ ሰዓት ይሰጠዋል። ለዚህ ነው በመጽሐፍ ቅዱስ ጌታ እግዚአብሔር “…ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም”(ኤር. 29፡11) በማለት የሚናገረው። ስለዚህ አሳባችንን ከእርሱ አሳብ ጋር አንድ እንዲሆን መጸለይ እንጂ እርሱን ወደ እኛ አሳብ ለማምጣት መታገል የለብንም ማለት ነው።
እግዚአብሔር አምላክ ገና ሳንለምነው የምንፈልገውን አውቆ የሚሰጠን አምላክ ስለመሆኑና የለመነውንም ነገር እንዳገኘነው እንድንቆጥር እንዲህ በማለት ያስተምረናል “...ስለዚህ እላችኋለሁ፤ የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፤የሆንላችሁማል”(ማር.11፡24)
ይህን ሁሉ የተስፋ ቃል በልባችን ውስጥ ካስቀመጥን፤ የእግዚአብሔር መልስ በእነዚህ በሦስት አይነቶች ወደ ህይወታችን ሊመጣ እንደሚችል መገንዘብ እንችላለን፡-
1. በጠየቅነው ዕለት ወይም በፍጥነት፡- እግዚአብሔር አምላክ ለጠየቅነው ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ሊሰጠን ይችላል። ይህ ከሆነ በእርሱ ላይ ያለንን እምነት እንድናጠነክር ፈቃዱ ሆኗል ማለት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ለጥያቄያቸው ፈጣን ምላሽ የተሰጣቸው ሰዎች አሉ። የመቶ አለቃው ልጁን እንዲፈውስለት ወደ ጌታ ቀርቦ “ጌታ ሆይ...ቃል ብቻ ተናገር ብላቴናዬም ይፈወሳል” (ማቴ.8፡8) ብሎ ሲማጸነው ወዲያውኑ ነበር የመለሰለት። ይህም የሆነበት ምክኒያት የመቶ አለቃው ከመጀመሪያው በጌታ ላይ እምነት ስለነበረው ያንኑ ሊያጠናክርለት ስለፈቀደ ነው። ከጌታ ቀኝ ተሰቅሎ የነበረው ጥጦስም የሆነውን ሁሉ ከተመለከተ በኋላ ክርስቶስ እውነተኛ የባህሪ አምላክ መሆኑን ሲያረጋግጥ “ጌታ ሆይ፡- በመንግስትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ” ብሎ ሲጠይቀው ጊዜ ሳይወስድ ወዲያውኑ ነበር “እውነት እልሀለሁ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ያለው(ሉቃ.23፡43) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን የሰዎችን የአጋንንትንም ልመና በፍጥነት የመለሰበት ጊዜ ነበር። ክርስቶስን አይተው እንዳያጠፋቸው ስለተጨነቁ “ወደ እሪያው መንጋ ስደደን”(ማቴ.8፡31) ብለው ሲለምኑት እንዲገቡ ፈቅዶላቸዋል።
በሽተኞችን፤ ታመው የአልጋ ቁራኛ የሆኑትን፤ የተሸከማቸውን አልጋ ተሸክመው እንዲሄዱ አድርጓቸዋል።እኛስ በህይወታችን ስንት ጊዜ እግዚአብሔር በፍጥነት መልሶልን እኛ ግን እረስተነው ይሆን? ብዙ ሰዎች ታመው አልጋ ላይ ሲሆኑ፤ ወይም በጭንቀት ውስጥ ሲወድቁ እግዚአብሔርን ይማጸኑና እርሱም ከበሽታቸው ሲፈውሳቸው፤ ከጭንቀታቸው ሲላቀቁ ይረሱታል። በእርግጥ የሰው ልጅ ብዙ ጊዜውን የሚያሳልፈው እግዚአብሔር ወደ ፊት የሚሰጠውን ነገር በማሰብ ወይም ደግሞ እርሱ የከለከለውን ነገር በማሰላሰል እንጅ እስካሁን ስለተደረገው ነገር በማመስገን አይደለም። የተደረገልን ነገር በሙሉ በእኛ ኃይልና ብርታት ከመሰለንና ለእርሱ የሚገባውን ድርሻ ለእኛ የምናደርግ መሆናችንን ካወቀ ወይም ደግሞ በእርሱ ላይ ያለንን ትእግስት መፈተን ከፈለገ እግዚአብሔር ጸሎታችን የሚመልስልን በሚከተለው አማራጭ ይሆናል።
2. ከብዙ ጊዜ በኋላ ዘግይቶ ሊመልስልን ይችላል፡- ይህ የሚሆነው ደግሞ እግዚአብሔር የእኛን ትእግስት መፈተን የፈለገ እንደሆን ነው።ለአብርሃም “በዘርህ አሕዛብ ይባረካሉ” ካለው በኋላ እጅግ ዘግይቶ በእርጅናው ጊዜ ነው ይስሀቅን የሰጠው። የአባታችን የአብርሃም ትእግስትም በዚህ ተፈትኗል። አብርሃም “የእግዚአብሔር መልስ ዘገየብኝ፤ ሌላ አማራጭ ልፈልግ” ብሎ ዘወር ቢል ኖሮ የብዙዎች አባት ባልተባለም ነበር።
እግዚአብሔር መልሱን የሚያዘገዬው ካለ እርሱ ምንም ማድረግ እንደማንችል ሊያስገነዝበን ሲወድ ነው።“ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉም” (ዮሐ15፡5) ብሏልና። አባታችን አዳም ከገነት ከተባረረ በኋላ በራሱ ጥረት ወደ ገነት ለመመለስ ሞክሮ ነበር። እግዚአብሔር ግን ይህ የፈጣሪን ሥራ እንደሚጠይቅ ነግሮት ከአምስት ሽህ አምስት መቶ ዘመን በኋላ ከልጅ ልጁ ተወልዶ እንደሚያድነው ቃል ገባለት። ስለዚህ አባታችን አዳም ያን ሁሉ ዘመን የእግዚአብሔርን መልስ በሲዖል ውስጥ ሆኖ መጠበቅ ነበረበት። በመሠረቱ ይህ ዘመን በሰው ዘንድ የረዘመ ይምሰል እንጂ በእግዚአብሔር አቆጣጠር ግን አምስት ቀን ተኩል ብቻ ነው።አባታችን ሙሴም እስራኤላውያንን እየመራ ከግብፅ ያወጣቸው ለአገልግሎት ከተጠራ ከአርባ አመት በኋላ ሰማኒያ ሲሞላው ነበር። አርባ አመት ሙሉ ግን በሲና በርሃ እጅግ አስቸጋሪ በሆነው ሙቀት ውስጥ የዮቶርን በጎች ይጠብቅ ዘንድ ግድ ነበር።(ዘጸ 4፡18)
3. ምንም ላይመልስልን ይችላል፡- ላቀረብነው ልመና ምንም አይነት ምላሽ ካላገኘን፤ ያ ማለት እኛ ከጠየቅነው ጥያቄ በላይ የተሻለ ነገር አስቦልናል ማለት ነው። እኛ ሰዎች ደካሞች እንደመሆናችን የሚጎዳንና የሚጠቅመንን ለይተን ማወቅ ስለማንችል አጥብቀን የፈለግነው ነገር ምላሹ ከቀረ፤ ሌላ የተሻለ ነገር እግዚአብሔር እያዘጋጀልን እንደሆነ እንመን።
በእርግጥ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ሳያውቁት የሚጠፉበትን ነገር ወይም ደግሞ ሌሎችን የሚጎዳ ነገር ሊለምኑ ይችላሉ። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር በሰዎች ጥፋት ተባባሪ ስለማይሆን “ይህ አይሆንም!” ሊለን ይችላል። የዘብዴዎስ ልጆች እናት ያቀረበችው ልመና ልጆቿን ለመስቀል ሞት የሚያበቃ ስለነበር የተሰጣት ምላሽ “የምትለምኑትን አታውቁም”(ማቴ.20፡22) የሚል ነበር።
ይህን ሁሉ የእግዚአብሔር የአሰራር መንገዶች ከተገነዘብን የእርሱን መልስ ስንጠብቅ ምን ምን ማድረግ ይኖርብናል የሚሉትን ነጥቦች ደግሞ እንደሚከተለው እንመልከት፡-
1.በእምነት መኖር
እግዚአብሔር አምላክ ሰምቶ እንዳልሰማ አይቶም እንዳላዬ ዝም የሚል አምላክ አለመሆኑን ማመን አለብን። እርሱ የሚሰማ የሚመልስም ነው እንጂ።እርሱ የፈጠረን አምላካችን ስለሆነ የልባችን ምኞትና መሻት ቁልጭ ብሎ ይታየዋል።
የእግዚአብሔርን መልስ በእምነት ውስጥ ሆነው ከጠበቁ ሰዎች ውስጥ ምንጊዜም የሚጠቀሰው አባታችን አብርሃም ነው። እግዚአብሔር የማያደርገውን የማይናገር የተናገረውን ደግሞ የማያስቀር አምላክ መሆኑን አብርሃም ጠንቅቆ ያምን ነበር። ስለዚህ የእግዚአብሔር መልስ ቢዘገይም ሊተወኝ ነው ብሎ አልፈራም አልተጨነቀምም።ሰዎች ፍርሃት የሚይይዛቸው እምነታቸው ሲጎድል ነው። ጌታችን ልጁ ለሞተችበት ለምኩራቡ አለቃ “እመን ብቻ እንጂ አትፍራ”(ማር5፡36) ብሎ ያረጋጋው በእርሱ ላይ ያለን እምነት የጸና ይሁን እንጂ ለእርሱ ምንም የሚሳነው ነገር እንደሌለ ሲገልጽለት ነው።
ችግርና መከራ ሲገጥመን እግዚአብሔር እንደሚረዳንና እንዲያውም ለእኛ በጣም ቅርብ የሚሆነው በዚህ ጊዜ መሆኑን ማመን አለብን።ዳንኤል የእግዚአብሔርን መልአክ ያየው እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ በወደደቀበት ወቅት በአንበሶች ጉድጓድ ውስጥ ነው። አናንያ፤አዛርያና ሚሳኤልም መልአኩን ያዩት በእሳት ውስጥ ሆነው ነው። እርሱ የእኛ ጭንቀት ተካፋይ ስለመሆኑ ነቢዩ ኢሳይያስ “በጭንቃቸውም ሁሉ እርሱ ተጨነቀ”(ኢሳ63፡9) በማለት ተናግሯል።እኛ ስንጨነቅ፤በዳር ሆኖ የሚያየን ሳይሆን አብሮን የሚጨነቅ አምላክ እንዳለን ስናስብ ምን ያህል ልባችን በደስታ ይሞላ ይሆን? ስለዚህ የእግዚአብሔርን መልስ ስንጠብቅ በእርሱ ላይ ያለን እምነት የተደላደለና የማይነቃነቅ መሆን ይኖርበታል።(1ቆሮ 5፡58)
2.በተስፋ
ክርስትና በተስፋ የሚኖሩት ህይወት ነው። ክርስቲያንም የሚኖረው ከሚታዩት ነገሮች በላይ ስለሆነ በዚህ አለም እያለ በሚያጣቸው፤ሀላፊ ጠፊ በሆኑ ነገሮች ተስፋ አይቆርጥም። በሥጋዊውም ሆነ በመንፈሳዊ ህይወት የሚያስፈልገንን ነገር ጠይቀን መልሱን የምንጠብቀው በተስፋ ነው። አንዳንድ ጊዜ የወደፊቱ ህይወታችን ድቅድቅ ጨለማ የዋጠው መስሎ የሚታየን ጊዜ ይኖራል። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር አምላክ የተናገራቸውን የተስፋ ቃላት በህሊናችን መድገም በቃላችን ማስታወስ ይኖርብናል። “በህይወትህ ዕድሜ ሁሉ... አልጥልህም፤አልተውህም”(ኢሳ1፡5) “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና...አትፍራ”(ሐዋ.18፡10) እግዚአብሔር አምላክ ለጥቂት ጊዜ የተወን ቢመስልም ለዘለአለሙ ግን ይሰበስበናልና ተስፋችን እርሱ ብቻ ሊሆን ይገባል። እርሱን ተስፋ ያደረገ ሰው ከቶውንም ቢሆን አይወድቅምና።
በአንድ ቀን ውስጥ ጨለማና ብርሃን እንደሚፈራረቁ ሁሉ በሰው ልጅ ህይወትም ፈተናና ደስታ ይፈራረቃሉ።ስቅለት እንዳለ ሁሉ ፋሲካም ይኖራል፤ ስለዚህ በስቅለት ያዘነ የተከዘ ሰው በፋሲካው ደግሞ ይደሰታል። በስቅለት ካላለፉ በቀር ስለፋሲካ ማውራት እንደሚከብደው ሁሉ ደስታም ያለ ፈተና ሊመጣ አይችልም። ለዚህ ነው ሐዋሪያው ያዕቆብ በመልእክቱ “ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት”(ያዕ.1፡2) ያለው። ይህ የተስፋ ቃል የተነገረው ጽኑ የሆነው መከራችን አስከትሎ የሚያመጣው በረከት ስላለ ነው። የገጠመን አስጨናቂ ፈተና ደስታን እንደሚያመጣልን ተስፋ የምናደርግ ስንቶቻችን እንሆን?
3.በፍቅር
ቀድሞ ስናደርግ እንደነበረው ሰውንም እግዚአብሔርንም መውደድ፤ ለሁሉም የሚገባውን ክብር መስጠት የእርሱን መልስ ስንጠብቅም መቀጠል አለበት። ዮሴፍ ያለ ኃጢአቱ ስለ ታሰረ፤ በእስር ቤት ሆኖ የእግዚአብሔርን መልስ ይጠብቅ ነበር።ነገር ግን በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ እንኳን በእስር ቤት ውስጥ እግዚአብሔርንም ሰውንም በፍቅር ያገለግል ነበር እንጂ ድሮ ያደርግ የነበረውን ነገር አላቋረጠም። ብዙ ሰዎች ግን የጸሎታቸው ምላሽ ሲዘገይ ቀድሞ ያደርጉ የነበሩትን ነገሮች እርግፍ አድረገው ይተዋሉ። በፊት ከቤተ ክርስቲያን የማይለዩት፤ በቀን ሁለት ጊዜ የሚጸልዩት አሁን ጨርሰው ይጠፋሉ፤ ከጸሎትም ይሸሻሉ። ምክኒያታቸውን ሲገልጹም እግዚአብሔር እንደረሳቸው፤ ለጸሎታቸውም ምላሽን እንዳጡ ይናገራሉ። እነዚህ ሰዎች የዘነጉት ነገር ቢኖር እግዚአብሔር አምላክ ማንንም እንደማይረሳ ነው። “ሴት ከማህፀንዋ ለተወለደው ሕፃንዋ እስከማትራራ ድረስ ልትረሳ ብትችልም” እርሱ ግን ፈጽሞ ሰው እንደማይረሳ የተናገረ አምላክ ነው።(ኢሳ.49፡15) የተናገረውን የማያስቀር አምላክ በመሆኑም ሙሴ መልኩን ለማየት ተመኝቶ ሞት ቢቀድመውም ከሞት አስነስቶ ከመቃብር አውጥቶ የተመኘውን ፈጽሞለታል። ለዚህ የፍቅር አምላክ እኛም የሚፈለግብንን ምስጋና ልናቀርብለት ይገባል እንጂ የእግዚአብሔር መልስ ዘገዬ ብለን በእርሱ ላይ ልንነሳሳ አይገባም። ለበጎ ቢያዘገየውም ልመናችንን አያስቀረውምና።
ስለዚህ ሰማይና ምድር ቢያልፉም እነርሱ ጸንተው የሚኖሩትን፤ ሦስቱን የክርስትና ሃይማኖት የእምነት ምሰሶዎች “እምነትን፤ተስፋን፤ፍቅርን”(1ቆሮ.13፡13) አንግበን፤ከሁሉም በሚበልጠው በፍቅር ከአምላካችን ጋር ተሳስረን፤ ከፊት ለፊታችን የሚጠብቀንን ሩጫ በትእግስት እንሩጥ። ለአባቶቻችን የተለመነ አምላክ ለእኛም መሻታችን ይፈጽምልናልና እመነታችንን አጽንተን የ እርሱን መልስ እንጠብቅ። እርሱን ተስፋ አድርጎ ያፈረ የለምና ተስፋችንንም በእርሱ ላይ እንጣለው። “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ያለቀ የተቆረጠ ነገርን በምድር መካከል ሁሉ ይፈጽማል”(ኢሳ 10፡23) ከእኛ የራቀ ቢመስለንም ምን ጊዜም ከአጠገባችን መሆኑንም አንዘንጋ። አንድያ ልጁን ሳይሳሳ የሰጠን አምላክ የእኛን ልመና እነዴት አይቀበለን?
ወስብሃት ለእግዚአብሔር።
ዲን. ፍቅረሥላሴ አቢይ
(ስቶክሆልም፤ የካቲት 30፤2003)
Subscribe to:
Posts (Atom)